የ2019 አዲስ ዓመት ገበያ ቅኝት፡ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቶበታል
በዕንቁጣጣሽ በዓል ዋዜማ የአዲስ አበባ ገበያዎች ከወትሮው የተለየ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እና የግብይት ውጥረት አስተናግደዋል። በከተማዋ በሚገኙ እንደ ፣ አቂቃ፣ ኮልፌ እና ካራ (ኮተቤ) የመሳሰሉ ታዋቂ የቁም እንስሳት ማዕከላት፣ በዓሉን አስመልክቶ የቀረቡት የእንስሳት ዋጋ ከቀደምት በዓላት በተለየ መልኩ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። እነዚህ ቦታዎች በተለይም በበዓላት ወቅት እጅግ በጣም በርካታ የእርድ እንስሳት የሚቀርቡባቸው ዋና ዋና ማዕከላት […]
በዕንቁጣጣሽ በዓል ዋዜማ የአዲስ አበባ ገበያዎች ከወትሮው የተለየ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እና የግብይት ውጥረት አስተናግደዋል። በከተማዋ በሚገኙ እንደ ፣ አቂቃ፣ ኮልፌ እና ካራ (ኮተቤ) የመሳሰሉ ታዋቂ የቁም እንስሳት ማዕከላት፣ በዓሉን አስመልክቶ የቀረቡት የእንስሳት ዋጋ ከቀደምት በዓላት በተለየ መልኩ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።
እነዚህ ቦታዎች በተለይም በበዓላት ወቅት እጅግ በጣም በርካታ የእርድ እንስሳት የሚቀርቡባቸው ዋና ዋና ማዕከላት እንደመሆናቸው መጠን፣ የዘንድሮው የገበያ ሁኔታ ከባድ የኑሮ ውድነት የታየበት ሆኗል።
በነዚህ ታዋቂ የገበያ ማዕከላት ካፒታል ባደረገው ምልከታ የቀንድ ከብቶች ዋጋ ከፍተኛ አኃዝ ይዞ መገኘቱን ለመታዘብ ተችሏል። ትልቅ የሚባሉት የእርድ ከብቶች እስከ 200,000 ብር ሲሸጡ፣ ዝቅተኛዎቹ ደግሞ በአማካይ ከ90,000 ብር ጀምሮ ተጠቃሚውን እየተፈታተኑ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል የአዲስ ዓመት የዶሮ ገበያ ከፋሲካ በዓል ጋር ሲነፃፀር ጨምሯል። መጠናቸው እንደ ሁኔታው የሚለያይ ሲሆን፤ ዝቅተኛው የዶሮ ዋጋ 1,400 ብር ሲሆን ከፍተኛው እስከ 3,500 ብር እየተጠራ ነው። ይህም ፋሲካ በዓል ላይ ከነበረው 1,300 ብር አማካይ ዋጋ ጋር ሲታይ የዕድገት ምጣኔውን ያሳያል። ከዕለት ተዕለት ፍጆታዎች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የዕቁላል ዋጋም አሻቅቦ የሀበሻ (የአገር ውስጥ) ዕቁላል 32 ብር፣ የፈሪንጁ (የውጭ/የድብልቅ) ደግሞ እስከ 28 ብር እየተሸጠ ነው።
ሸማቾች ለካፒታል እንዳሉት የዋጋው ጭማሪ በእዚህ ልክ ይሆናል ተብሎ ያልተጠበቀ እና ኪሳቸውን የፈተነ መሆን አስረድተዋል። በዓሉን በቻሉት አቅም ለማሳለፍ ሲጥሩ፣ የዶሮ እና የሌሎች የፍጆታ ዕቃዎች መወደራቸው ከገቢያቸው ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ጥሏቸዋል። በሌላ በኩል የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ዋጋው እንዲጨምር የተደረገው በራሳቸው ፍላጎት እንዳልሆነ ይገልራሉ። አሁን ፈታኝ ከሆነው የመኖ ዋጋ እና ከሌሎች ወጪዎች አንፃር ምንም ማድረግ ስለማንችል ነው ጭማሪውን ያደረግነው ሲሉ የንግዱን እውነታ ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ ስታቲክስ አገልግሎት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 15.1 በመቶ ደርሷል። የምግብና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች ዋጋ 14.9 በመቶ የጨመሩ ሲሆን፤ በዋናነት አትክልት 12.1 በመቶ፣ ስጋ 22.6 በመቶ፣ የወተት ተዋፅኦዎች እና እንቁላል 18.7 በመቶ፣ ፍራፍሬ 19.1 በመቶ፣ ዘይት እና ቅቤ 18.8 በመቶ፣ እንዲሁም ስኳር እና የምግብ ምርቶች 16.8 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል።






